ሰሞኑን በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች እየደረሰ ያለው ሁኔታ በጣም የሚያሳዝን ሆኗል። ይህ ነገር ሲከሰት አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከአንድ አመት በፊት ተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጥሮ እኛም በወቅቱ መልእክት አስተላልፈን ነበር።
ማሳሰቢያ፥ምክር፤ ተመልሶ እንዳይደገም። ታዲያ እንዴት ተመሳሳይ አደጋ ሊደገም ቻለ? አሁን ተባብሶ የብዙ ኦሮሞ ወገኖቻችን ህይወት ሊቀጥፍ ችሏል። ይህ ደግሞ እጅግ በጣም የሚያሳዝንና አሰቃቂ ነገር ነው።
በመጀመሪያ ለሟች ቤተሰቦች መጽናናት የቆሰሉትም እንዲያገግሙ እንጸልያለን፤ እግዚአብሔር መጽናናቱንና ብርታቱን ይስጣቸው።
ጉዳዩ ከማስተር ፕላኑ አልፎ የተጠራቀመ የመልካም አስተዳደር እጦትና የመብት ጥያቄዎችን ብሶት ያካተተ ሆኗል። በዚህ ጉዳይ ላይ በፍጥነት እርማት ካልተካሄደ ከፍተኛና ያልተጠበቀ አደጋ በሀገሪቷ ላይ ሊደርስ ይችላል። ይሄ ነገር ተባብሶ ከዚህም የባሰ የብዙ ወገኖቻችንን ህይወት ከመቅጠፉ በፊት ይታሰብበት።
የሰው ነፍስ ያለ አግባብ ያጠፉ፥ ከመጠን በላይ ሀይል የተጠቀሙ ሁሉ በህግ ይጠየቁ።
መንግስት ከህዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች በአግባቡ መልስ ይስጥ። ጉዳዩ በግልጽ ውይይት የሚፈታ በመሆኑ ከህዝቡና በሀገር ቤት ካሉ ህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ውይይት ይደረግ። ባለፈው መንግስት ቃል እንደገባው በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተመካከርን እንሰራለን ብሏልና ቃሉን ይፈጽም። Read more