በኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች ዛሬም ተቃውሞ ቀጥሏል

0
394

feneral(VOA) ከአምቦ ከተማ ባለፈው ሃምሌ ወር ታስሮ በአዲስ አበባ እስር ቤት ሳለ ታሞ ሆስፒታል ህይወቱ እንዳለፈ የተገለጸው ተማሪ አብደታ ኦላንሳ ቀብር ዛሬ በአምቦ ከተማ ተፈጽሟል። የጸጥታ ሃይሎች ቀብር ሥነ ስርዓቱን ለማስተጓጎል ድብደባና እስር ፈጽመዋል። ትናንት አስከሬኑን ለመቀበል ተኩሰው የገደሉትም አለ ብለዋል።

ባለፈው ሐምሌ ወር ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ ተወስዶ ታስሮ እንደነበርና ታሞ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ህክምና ላይ ሳለ ህይወቱ እንዳለፈ የተነገረው ተማሪ አብደታ ኦላንሳ ቀብር ዛሬ አምቦ ከተማ ተፈጽሙዋል። በስልክ ያነጋግርናቸው ነዋሪ አቶ ጉቱ ትናንት ማታ የወጣቱን አስከሬን ለመቀበል በወጣ ህዝብ ላይ የጸጥታ ሃይሎች ድብደባ አድርሰዋል። ወደሰማይ ሲተኩሱም ነበር። አንድ ሰው በጥይት ተመትቶ ተገድሉዋል ብለዋል።

የአምቦው ነዋሪ አስከትለውም ዛሬ በቀብሩ ላይም እንዲሁ የከተማው ነዋሪ በብዛት ወጥቶ እንዳይቀብረው ለማስተጉዋጎል ወታደሮች በተለይ ወጣቶችን መኪና ላይ እየጫኑ ወስደዋቸዋል ብለዋል። ወደቀብሩ ጉዞ ላይ የነበረ ወጣት በጥይት መገደሉን ገልጸውልናል።

ትናንትና ደግሞ በአምቦ ዩኒቨርስቲ አዋሮ ግቢ አጠገብ የአንድ ወጣት አስከሬን ተገኝቱዋል ብለዋል አቶ ጉቱ

የአምቦ ወረዳ ኣስተዳዳሪ ኣቶ አሰፋ ሂርኮ ኣምቦ ውስጥ ተገደሉ የተባለውን ኣስተባብለዋል። Listen

ጃለኔ ገመዳ ኣነጋግራቸው ነበር ። “ባለው መረጃ አምቦ ውስጥ የተገደለ ሰው የለም አዲስ አበባ ከተማ ታሞ የሞተ ሰው ኣአስከሬኑ አምቦ ገብቶ ዛሬ ተቀብሩዋል ። ለበለጠ መረጃ የአምቦ ከተማ ከንቲባውን አነጋግሩ” ሲሉ ቢመሩዋትም ከንቲባ ዱጋሳ ኦሉማ በእጅ ስልካቸው በተደጋጋሚ ተደውሎ ኣላነሱትም።

 

አዲስ አበባ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሞቶ ዛሬ ተቀበረ ስለተባለው ወጣት አብደታ ኦላንሳ ጉዳይ ሆስፒታሉ መዝገቡን ተመልክቶ ነገ ማብራሪያ ሊሰጥ ቀጠሮ ሰጥቱዋል

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ሶራ ሃለኬ ባገኘው መረጃ ደግሞ ፌደራል ፖሊሶች የተማሪዎች መኝታ ቤቶች እየገቡ ጭካኔ የተመላበት ድብደባ አካሂደዋል ብዙ መቶዎች አስረው ወስደዋል

ስሜን ኣትግለጡ ያለው ተማሪ ገልጾለታል። ተማሪዎች ያሉትን ለማጣራት ወደከተማዋ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ደውሎ እንዳልተሳካለት ሶራ በዘገባው አመልክቱዋል

በምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ ደግሞ የከተማው መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች “የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት የታሰሩ ተማሪዎች ይፈቱ” “ ግድያው ይቁም “ በማለት ትናንትናና ዛሬ ሰልፍ ወጥተዋል ሲሉ “ ስማችንን እንዳትገልጹብን” ያሉ ተማሪዎች ለቱጁቤ ኩሳ ገልጸውላታል።

በሰላም ነበር ሰልፉ የሚካሄደው የመንግሥት ሃይሎች በተኑት ፡ የተወሰኑ ተማሪዎች ተደበደቡ ፡ የታሰሩም አሉ ያለው ተማሪ እኔም ራሴ ከተደበደቡት አንዱ ነኝ ብሉዋል።

“የሃሮማያ እና የጅማ ተማሪዎች እንዲሁም በኣምቦ ተማሪዎች መገደላቸውን በመቃወም ፡ ድርጊቱ ይቁም ትግላችን ይቀጥላል ብለን ድምጻችንን ስናሰማ ነበር” ሲል ገልጹዋል።’

የሻሸመኔ ከተማ የአስተዳደር እና ደህንነት ሐላፊ ኣቶ ስንታየሁ ጥላሁን ግን ሃሰት ነው ይላሉ ።

“ሰልፍ የወጣ የለም። ሰልፍ ማካሄድ ተፈቅዱዋል ፡ ግን የወጣም የለም የታሰረም የለም፡ ተማሪዎች እየተማሩ ናቸው። መማር የፈለገ ይማራል ፡ የማይፈልገውን ግን አናስገድድም መብቱ ነው።” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ስንታየሁ አንዳንድ ጥያቄ ያነሳ ሊኖር ይችላል ብለው ነበርና ቱጁቤ ምን ጥያቄ ነው ያነሱት? ብትል “ማለት የጠየቁት እኮ ነገር የለም ቢሮችን የደረሰው መረጃ የለም ከተማውም ሰላም ነው” እንዳሉዋት አክላ ጠቅሳለች።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ዛሬም የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች እንደቀጠሉ መሆናቸውን ከተለያዩ ከተሞች የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ ቆንጂት ታዬ ታቀርበዋለች።

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here