By Jawar Mohammed,
Translation from English to Amharic by Yaya Beshir
በወያኔው ቃላቀባይ ጌታቸው ረዳ የተሰጠውን መግለጫ ኣነበብኩት።
በኣጋዚ ሃይል ላይ የተወሰደው ጥቃት በታጠቀ ቡድን የተከናወነ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ በከፊል እውነት ነው። ነገር ግን ማነው ያ የታጠቀ ቡድን? ለመሸሸግ የተሞከረው ሃቅ እንዲህ ነው። የፌዴራል ፖሊስና የኣጋዚ ወታደሮች በክልሉ የሚሊሻና የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ (ፈጥኖ ደራሽ) የተቀናጀ ሃይል ተገድለዋል። ለዚህ ማስረጃው ደግሞ የኣጋዚ ሃይሎች በርካታ የኦሮምያ ልዩ ፖሊስ መኮንኖችን መግደላቸው ነው። በኣጋዚ ከተገደሉት የኦሮምያ ፖሊስ መኮንኖች መካከል ሙስጠፋ ሃሰን (የኣካባቢው ተወላጅና ነዋሪ) እና ረመዳን ኣብደላ (ከምስራቅ ሃረርጌ) ናቸው። እነዚህ ሁለቱ ግለሰቦች በተሳሳተ መልኩ በሲቪል ሰርቫንትነት ተገልጸዋል። (ምንጩ ሲናገር ‘ለመንግስት የሚሰሩ’ በማለት ሲገልፅ ኣኛ ደግሞ በሲቪል ሰርቫንትነት ወስደነው ነው።)
1. ሁለቱን ሰላማዊ ሰልፈኞች የገደሉትን የመጀመሪያዎቹን የኣጋዚ ቡድን ኣባላት ትጥቅ ያስፈቱት የኦሮምያ የፀጥታ ሃይሎች (ሚሊሻና ፖሊስ) ናቸው። ተጨማሪ የፌዴራል ጦር ሃይል ደርሶ የተማረኩትን ሁለቱን የኣጋዚ ጦር ኣባላትን ለማስለቀቅ ጥቃት ሲፈፅም የኦሮምያ ፖሊስ ለኣንዳንድ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ የጦር መሳሪያ በማቀበል ባደረገው የኣፀፋ ጥቃት 11 የኣጋዚ ወታደሮች ተገደሉ። ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ መኮንኖች ህዝቡ ኣስከሬናቸውን ተመልክቶ መለየት የቻለው ብቻ ናቸው። ከሁለቱም ወገኖች የተገደሉትና የቆሰሉት ወደ ኣዋሳና ፍንፊኔ ሆስፒታሎች ተወስደዋል። እነዚህ ‘የታጠቁ ቡድኖች’ የተባሉት ከሩቅ የመጡ ባእዳን ኣማፂዎች ሳይሆኑ በራሱ በስርኣቱ መሪዎች የታጠቁና የተሰማሩ የደህንነት ኣካላት ናቸው።
2. ቃላቀባዩ ኣክለውም ሰላማዊ ሰልፈኞቹ የመንግስት እርሻ እንዳወደሙ ተናግረዋል። ልክ ነው ሰላማዊ ሰልፈኞቹ እርሻና ሌሎች ንብረቶችን ኣውድመዋል። እነዚህ እርሻዎች ቀደም ሲል የመንግስት የነበሩ ቢሆኑም ሁዋላ ላይ ግን ለውጭና ለህወሃት ኩባንያዎች ተሽጠዋል። እናም ሰልፈኞቹ ‘መሬታችንን ቀምታችሁኣል፣ እኛ ስንራብ የስንዴውን ምርት ወደ ሌላ ቦታ ጭናችሁታል!’ እያሉ መፈክር ሲያስተጋቡ ተሰምተዋል። በነገራችን ላይ ምእራብ ኣርሲ/ምስራቅ ሸዋ በረሃቡ ክፉኛ ከተጎዱት ኣካባቢዎች መካከል ይጠቀሳሉ። 40% የሚሆነው የኣካባቢው ህዝብ ኣስቸኩዋይ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ነው።
3. የስርኣቱ ቃላቀባይ በመቀጠልም ለግጭቱ መንስኤ ሃይማኖታዊ እንደምታ ሰጥተውታል። ይህ ጨርሶ ውሸት ነው። ኣንድም የኣካባቢው መስጊድም ሆነ ቤተክርስቲያን ጥቃት ኣልተፈፀመበትም። በኣካባቢው ምንም ኣይነት ሃይማኖታዊ ኣለመግባባት ኣልነበረም። የኛ ስጋት የነበረው ኣካባቢው ከደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጋር ስለሚዋሰን የሰርኣቱ ወኪሎች የብሄር ግጭት ይጭሩ ይሆናል የሚል ነበረ። ያ ራሱ ኣልተከሰተም።
ለስርኣቱና ለውጭ ደጋፊዎቹ የምለግሰው ምክር ኣለ። ከእውነት ጋር ተጋፈጡ። ከውጭ የመጡ ግጭት ቀስቃሾችን ኣይደለም እየተዋጋችሁ ያላችሁት። ህወሃት በሚያደርገው ወሰን የሌለው ጣልቃ ገብነት ሳቢያ በኦሮምያ የኣስተዳደርና የደህንነት ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ዘቅጧል።
1. ህወሃት ወያኔ የክልሉን ፕሬዝዳንት ከስልጣን ካነሳው ወር ያለፈው ሲሆን ፕሬዝዳንቱ እስካሁን የት እንዳለ ኣልታወቀም። በሌላም ኣልተተካም። ክልሉ በዋና ስራ ኣስፈፃሚ እየተመራ ኣይደለም።
2. የኦሮሚያ ካቢኔ ላለፉት ሁለት ወራት ተሰብስቦ ኣያውቅም። በክልሉ ምንም ኣይነት የጋራ ስራ ኣስፈጻሚነት ውሳኔ እየተደረገ ኣይደለም። ትእዛዞች በቀጥታ እየተላለፉ ያሉት ከህወሃት ደህንነት ቢሮ ነው።
3. የኦህዴድ ስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴ ሁለቱንም ማለትም መደበኛና ኣስቸኩዋይ ስብሰባዎችን እንዳያደርግ ታግዷል።
4. የህወሃት ደህንነት ሃይል የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ ኣባላትን፣ የድፓርትመንት ሃላፊዎችንና የዞን ኣስተዳዳሪዎችን እንዳሻው ያዋክባል፣ ይደበድባል፣ ስማቸውን ያጠቁራል። ይህም ክልሉን የማስተዳደርን ስራ ኣስቸጋሪ ኣድርጎታል።
5. ጨፌ ኦሮምያ ላለፉት 4 ወራትና ከዛ በላይ ተሰባስቦ ኣያውቅም። በርካታ የጨፌው ኣባላት ወይ ታስረዋል ኣልያም የገቡበት ኣልታወቀም። ዳኞች፣ ኣስተዳዳሪዎችና የድፓርትመንት ሃላፊዎች ያለ ህጋዊ ኣካሄድ ከስራቸው ተወግደዋል።
6. ህወሃት የኦህዴድ ማ/ኮሚቴ ባለፈው የመጨረሻው ጉባኤው (ጃኑዋሪ 10-13?) ያቀረበውን ባለ 15 ነጥብ ጥያቄ ውድቅ ኣድርጎበታል። እነዚህ የቀረቡት ጥያቄዎች የፌዴራል ሃይሎች ከኦሮምያ እንዲወጡ፣ ኮማንድ ፖስት እንዲፈርስና ሌሎች (በሚቀጥሉት ቀናት እዚሁ ላይ የምናነሳቸውን) በርካታ ፖሊሲ ነክ ጥያቄዎችን ያካተቱ ነበረ።
ስለሆነም የህወሃት ኣመራሮችና የውጭ ደጋፊዎቻቸው በጥብቅ የሚመከሩት ጉዳይ ኣይናቸውን ከፍተው እውነታውን እንዲመለከቱ ነው። በኦሮሞ ተቃዋሚዎች፣ ተማሪዎች ወይም ዳያስፖራው ላይ ብቻ ሳይህን ባገር ቤትና በውጭ የሚገኘውን መላው የኦሮሞን ህዝብ ኢላማቸው ኣድርገዋል። ‘የታጠቀ ቡድን’ በማለት ከሩቅ የመጣ ኣማፂ ቡድን ኣስመስለው ለማቅረብ የሚሞክሩት ሃይል የገዛ የደህንነታቸው ኣካል ነው። እንዲሁም በእስላማዊ ኣክራሪነት ለመፈረጅ የሞከሩት የምስራቅ ሸዋ/ምእራብ ኣርሲ ወረዳዎች በኣመዛኙ የኣድቬንቲስት ክርስትና ተከታዮች ናቸው። ስለሆነም ፍረጃው ከእውነት የራቀ፣ ኢ-ሎጂካዊና ኣደጋም የሚያስከትል ነው።
ከዚህ ቀውስ ለመላቀቅ ኣንድ ብቸኛ መንገድ ነው ያለው። የተቃዋሚው ጎራና የመንግስቱ ኣካል የሆኑ የኦሮሞ ኣመራሮችን ኣድምጧቸው። የፌዴራል ፖሊስን ከኦሮምያ በማስወጣትና የኮማንድ ፖስት መዋቅሩን በማፍረስ መጀመር ትችላላችሁ። ከዚያም ሙሉ ስልጣን ለክልሉ መንግስት መልሱ። ከዚሁ ጎን ለጎን የጋራ መፍትሄ ለማፈላለግ ከኦሮሞና ሌሎችም ኣመራሮች ጋር ቁጭ ብላችሁ ተወያዩ።
ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ኣለመሆን በስርኣቱ፣ በቀንዱ ቀጣናና በማህበረሰቡ ላይ ኣደገኛ ውጤቶችን መጋበዝ ይሆናል። የኦሮሞ ህዝብ በኣገሪቷና በቀጣናው ኣስተማማኝ ሰላምና መረጋጋትን የማስፈን መብትና ፍላጎት ኣለው። ይሁንና በተጫነበት የጭቆናና የብዝበዛ ኣገዛዝ እንዲሁም በገዛ ኣገሩ ላይ ክብር በመነፈጉ ተዳክሞ ቆይቷል። ኣሁን ግን የሚገባውን ክብር ለማስመለስ በቁርጠኝነት ተነስቷል!!