የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርና 21 ተጠርጣሪዎች የሽብርተኝነት ክስ ተመሠረተባቸው

0
571

– ብዙ ሰዎች መሞታቸውና 122.3 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት መውደሙ ተጠቁሟል

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላንና የኦሮሚያ ከተሞች ዕድገት ፕላን በመቃወምና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች አመፅ በማስነሳት ጉዳት በማድረስ፣ የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 22 ተጠርጣሪዎች የሽብር ተግባር ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ሚያዝያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ሚያዝያ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ክሱን ለሚመረምረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያመለክተው፣ እነ አቶ በቀለ ገርባ ክስ የተመሠረተባቸው በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 35፣ 38፣ 32 (1ሀ) እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 1፣ 3፣ 4 እና 6 ተላልፈዋል በማለት መሆኑን አስፍሯል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ክሱን በሁለት ከፍሎ ያቀረበ ሲሆን አቶ በቀለ ገርባ፣ ጉርሜሳ አያኖ፣ ደጄኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላ፣ አብዲሳ ነጋሳ፣ ገላን ነገራ፣ ጭምሳ አብዲሳ፣ ጌቱ ግርማ፣ ፍራኦል ቶላ፣ ጌታቸው ደረጀ፣ በየነ ሩዳ፣ ተስፋዬ ሊበንና አሸብር ደሳለኝ በአንደኛው ክስ ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ለጊዜው ስማቸው ካልታወቁ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የፖለቲካ ድርጅት አባልና አመራር መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቱን እንደ ሽፋን በመጠቀም የፖለቲካ ሥልጣን በኃይል ለመያዝ በሚንቀሳቀሰው ኦነግ ውስጥ አባል በመሆንና ዓላማውን ለማሳካት በአገሪቱ ውስጥ ሁለትና ብጥብጥ እንዲነሳ፣ የሰው ሕይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላንና የኦሮሚያ ከተሞች የዕድገት ፕላን የኦሮሞ ሕዝብን ቋንቋና ባህል ከማጥፋቱም በተጨማሪ፣ የኦሮሞን ሕዝብ ከመሬቱ የሚያፈናቅል መሆኑን በመግለጽና የሥራ ክፍፍል በማድረግ፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችና ቀበሌዎች አመፅ እንዲነሳ በማድረጋቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች እንዲቋረጡ፣ በመንገዶች ላይ ጉዳት እንዲደርስና ቁጥሩ ያልታወቀ ሰው እንዲሞት፣ በ122 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንዲደርስና ከ122,394,391 ብር በላይ በመንግሥት፣ በግለሰቦችና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ንብረት ላይ ውድመትና ጉዳት መድረሱን ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ማስተር ፕላኑ ከመፅደቁ በፊት በቡራዩ ከተማ የሚኖሩ ወጣቶች እንዲነሳሱና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ፣ ትራንስፖርት እንዳይኖርና ትምህርት እንዲቆም ቅስቀሳ በማድረግ፣ እንዲሁም የኦነግ ልሳን ለሆነው የኦሮሞ ሚዲያ ኔት ወርክ (OMN) መረጃ በመስጠትና አመፅ በሁሉም የኦሮሚያ ከተሞች እንዲነሳ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል፡፡ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ኃላፊና የኦነግ አመራር ናቸው ከተባሉት ጃዋር መሐመድ ጋር በተደጋጋሚ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በመገናኘት፣ ገንዘብ እንዲላክ በማድረግና ማስተር ፕላኑን ሽፋን በማድረግ የሽብር አመፁን ሲያስተባብሩ እንደነበርም አክሏል፡፡

ተከሳሾቹ ስልክ በመደዋወል በሁሉም የኦሮሚያ ከተሞች ሕገወጥ ሠልፍና ተቃውሞ እንዲደረግ፣ በጉጂ በተለያዩ ወረዳዎች እንዲተገበር መንገድ በመዝጋት፣ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ላይ ረብሻና ብጥብጥ በማንሳት፣ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ ለማድረግ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ልሳን ለሆነው ኢሳት ሬዲዮና ቴሌቪዥንና ለጃዋር መሐመድ ሪፖርት ሲያደርጉ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡
አቶ በቀለ ገርባ ኦፌኮን ሽፋን በማድረግ ከእስር እንደተፈቱ ወደ አሜሪካ በመሄድ ከኦነግ አመራሮች ጋር ከተገናኙ በኋላ፣ ወደ አገር ቤት በመመለስ ከኦነግ የተቀበሉትን የአመፅ ተልዕኮ ኦሮሚያ ላይ ለማቀጣጠል አቶ ደጀኔ ጣፋን በአምቦ ከተማ፣ ጉርሜሳ አያናን በፊንፊኔ ዙሪያ ቡራዩ ከተማ፣ አዲሱ ቡላላን ቡሌ ሆራ አካባቢ ተሰማርተው አመፅ እንዲያነሳሱ መመደባቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገስጿል፡፡ በኦሮሚያ ዞኖች በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የኦፌኮ አባላት ድርጅቱን እንደ ሽፋን በመጠቀም የኦነግን የሽብር ተልዕኮ ለማሳካት ለአመፅ እንዲደራጁ በማድረግ፣ የመንግሥት መዋቅሮች እንዲፈርሱ፣ መንገዶች እንዲዘጉ፣ በፀጥታ ኃይሎችና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ጠቁሟል፡፡ በምዕራብ ሸዋ አምቦ፣ ግንደበረት፣ ጊንጪ፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ትምህርት ቤቶች፣ ቄሌም ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ፣ ቡራዩ፣ ሱልልታ፣ በተለያዩ አካባቢዎች አመፅ በማስነሳት የሰው ሕይወት እንዲጠፋ፣ የአርሶ አደሮችና ከተማ ነዋሪዎች ንብረት እንዲወድም፣ በእሳት እንዲጋይ፣ የኢንቨስተሮች ንብረት እግዲወድም አቶ በቀለ አመራር መስጠታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

ተከሳሾቹ በህቡዕ ተደራጅተው የሽብር ተግባር ወንጀል ለመፈጸም አባል ከሆኑ የአቃቂ ቃሊቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂና ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር በመሆን የቅስቀሳ ሥራዎችን ሲሠሩ፣ ወረቀቶችን በማሳተም ለመበተን ሲንቀሳቀሱ እንደነበር፣ በመቐለ ዩኒቨርሲቲና በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ከሚገኙ የሴል አባላት ጋር እየተነጋገሩ፣ ለቡሌ ሆራ፣ ሐረማያና መቱ ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኮ ከመስጠታቸውም በተጨማሪ አመፅ ቀስቃሽ ጽሑፎችን በአዲስ አበባ ሊበትኑ ሲሉ መያዛቸውን በክሱ አስፍሯል፡፡

ተከሳሾቹ በጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ፣ ጊንጪ ከተማ፣ ጀልዱ ወረዳ፣ ኤጀሬ ወረዳ፣ በሰሜን ሸዋ ወረጃርሶ አካባቢ መንገድ በመዝጋትና ሕፃናትን ከፊት በማሠለፍ አዋቂዎች ከኋላ በመሆን አመፁ እንዲቀጣጠል ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይተነትናል፡፡ ተከሳሾቹ በአመፁ ዋና ተሳታፊ መሆናቸውንም አክሏል፡፡
ሌሎቹ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ደግሞ አርጆ መርጋ፣ የሱፍ ዓለማየሁ፣ ኒካ ተክሉ፣ ገመቹ ሻንቆ፣ መገርሳ አስፋው፣ ለሚ ኤዴቶ፣ አብዲ ታምራት፣ አብዲሳ ኩመሳና ሀልከኖ ቆንጮና ሲሆኑ፣ በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ) እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1)ን በመተላለፋቸው ክስ እንደመሠረተባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ተከሳሾቹ የአገሪቱን ሕዝቦች አንድነት የማፈራረስና የኦሮሚያን ክልል ከፌዴሬሽን የመገንጠል ዓላማ ለማስፈጸም፣ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠርና ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ሕገ መንግሥታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማኅበራዊ ተቋማትን ለማናጋትና ለማፈራረስ በሚንቀሳቀሰው ኦነግ ውስጥ አባል በመሆን፣ ከድርጅቱ አመራሮች ጋር በመገናኘት፣ አባላትን በመመልመልና የተለያዩ መረጃዎችን ሲያስተላልፉ እንደነበርም አክሏል፡፡

ተከሳሾቹ በፌስቡክና በስልክ በመገናኘት የድርጅቱ አባል በመሆን፣ አባላትን በመመልመል፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ መረጃዎች በማስተላለፍ፣ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የተላከን 500 እና 400 ዶላር በመቀበል የተለያዩ የሽብር ተግባራትን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በክሱ ገልጿል፡፡

ሁሉም ተከሳሾች የኦነግን የሽብር ተልዕኮ ለማሳካት በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች ሁከትና አመፅ እንዲነሳ አመራር በመስጠት፣ በአመፁ ተሳታፊ በመሆን፣ የበርካታ ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ፣ በአካል ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ በመንግሥት፣ በሕዝብ ተቋማት፣ በመሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ በማስደረግና በማድረግ የሽብርተኝነትን ድርጊት ፈጽመዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ፣ ፍርድ ቤቱ ለተከሳሾቸ እንዲደርስ ካደረገ በኋላ ክሱን ለማንበብና በክሱ ላይ ተቃውሞ ካላቸው ለመስማት ለሚያዝያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here