ማሞ መዘምር— የነፃነት ነብይ

0
673

ቄሮን አፍርተሃል እና ሞትህ ከንቱ አልነበረም

ሰሞኑን በተከታታይ የሜጫ—ቱለማ እንቅስቃሴ እና ጉልግ ድርሻ ያላቸውን ሰዎች አነሳለሁ፡፡

እንቅስቃሴው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተዛመተ፣ መቶ አለቃ ማሞ መዘምር፣ ኢብሳ ጉተማ፣ ባሮ ቱምሳ፣ ዮሐንስ ለታ፣ መኮንን ገላን፣ ተዛ አሊ … ማሕበሩን ተቀላቀሉ፡፡ ከማሞ መዘምር በስተቀር፣ ሌሎቹ በሙሉ በ1968 ዓ.ም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መስራቾች ናቸው፡፡ በርግጥ እዚህ ባይዘረዘርም፣ የዚህ ማህበር አባላት የነበሩና በኋላ የኦነግ መስራቾች የሆኑ ብዙ አባላት አሉ፡፡ ከሰማዕቱ ባሮ ቱምሳ በቀር፣ ሌሎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስመ-ጥር የኦነግ አመራር ነበሩ፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ሜጫና ቱለማን በቀጥታ ከኦነግ መመስረት ጋር የሚያያይዘው፡፡

ከወጣቶች የማሞ መዘምርን ያክል የማህበሩን ክንፍ ስር-ነቀላዊ ያደረገ የለም፡፡ መቶ አለቃ ማሞ የኦሮሞ ታሪክ መፃፍ፣ በአፋን ኦሮሞ ስነ-ፅሁፎችን ማምረት የንቅናቄው ዋነኛ የርዕዮተ-ዓለም የጦር ግንባር አስመስሎት ነበር፡፡ “History of the oromo” የተባለ መፅሐፍ ፅፎ ያጠናቀቀ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ በ1967 ዓ.ም ቤቱ ሲበረበር ተገኝቶ ተወስዶበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማሞ፣ የአዲስ መንግስት ዕቅድ እና የአዲስ ህገ-መንግስ ረቂቅም አዘጋጅቶ ነበር፤ ይባስ ብሎ መሬት ለመሬት አልባው አራሽ፣ እንዴት እንደሚከፋፈል የሚዘረዝር ረቂቅ ሰነድም ጭምር አዘጋጅቶ ነበር፡፡

ማሞ ትግሉን ከከተማ እንቅስቃሴ የማሻገር ግብ ነበረው፤ ነፍጥ ካነሱ የተለያዩ ድርጅቶች ጋር ግንኑነት ነበረው፤ ከነዚህ ውስጥ ለባሌ ኦሮሞ አማፂ አመራሮች የፃፈውን ደብዳቤ እንመልከት፡-

“የሰው ዘር ታሪክ አንድ ነገር አስተምሮናል፤ ሞትን በመድፈር ለነፃነት (Freedom) እና ሉዓላዊነት (independence) የታገሉ ሁሉ አሸናፊ እንደሆኑ፡፡ በኢምፔሪያሊስቷ አሜሪካ የተደገፈውን የኢትዮጵያ ግዛተ-አፄ ጠቅላይነት ለመገርሰስ የሚደረገው በነፍስ ግቢና ነፍስ ውጪ መካከል ያለ ትግል፣ የተጨቆኑና የተዋረዱ ሚሊዮኖችን ነፃ ስለሚያወጣ የተቀደሰ ተግባር ነው፤ የጭቁኖች የተቋማዊነት መንገድ እና ንቃት ስር እየሰደደ መሄዱ እውን በመሆኑ ትግሉን የበለጠ ያቀጣጥላል፡፡ ከዚህ ቀደም ባደረግነው ውይይት እንደተረዳችሁት፣ የኦሮሞን ሕዝብ ንቃት ከፍ ለማድረግ የተቋቋመው የሜጫና ቱለማ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ልንደርስበት የምንችለውን ሁሉ ቅንጅት ለማምጣት ቀን ከሌሊት እየሰራ ያለ ተጨባጭ ተቋም ነው፡፡ በርግጥ ብርቱ (militant) የሆኑ አባላቱ የኦሮሞን ሕዝብ በሙሉ ምኞት እውን የሚያደርግ ብሄር አቀፍ (national-wide) ንቅናቄ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ እያንዳንዱን ኢንች የኦሮሞ መሬት በመከላከሉ ረገድ እስከ መጨረሻ የደም ጠብታ ድረስ የትጥቅ ትግላችሁን በጀግንነት ትገፉበት ዘንድ አደራ እላለሁ፡፡ አምፔሪያሊስቶች፣ ፅዮናዊነት እና በየአካባቢው ያለ ተቃውሞ ከሚያመጣው እንቅፋት በተቃራኒ ባሌን ለመከላከል የምታደርጉት ተጋድሎ በአሸናፊነት እንደሚወጣ አልጠራጠርም፡፡ ከናንተ ጋር በጀመርነው ግንኙነት ለመቀጠል የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡”

ይህ ደብዳቤ በአራት ምክንያቶች የተነሳ በጣም ወሳኝ ነው፤

1. በመጀመሪያ መስከረም 10 ቀን 1965 ዓ.ም መፃፉ ነው፤ በወቅቱ የነበረውን የማህበሩን ሁኔታ በቅጡ ያስረዳል፤

2. ሁለተኛ በማህበሩና በባሌ ኦሮሞ የትጥቅ ትግል አመራሮች መካከል የነበረውን ግንኙነት እንዲሁም የጋራ ጥረታቸውን እንዴት ማቀናጀት እንዳለባቸው የሚያደርጉትን ውይይት ያሳያል፡፡

3. ማህበሩ፣ የኦሮሞን ሕዝብ ከተቀረው ሕዝብ ጋር እኩል ለማድረግ በሰላማዊ መልኩ ቢታገልም፤ ሰላማዊ ትግሉ የተፈለገውን ውጤት ባያስገኝ እንኳ በሚል የትጥቅ ትግልን ከምርጫ ውጪ አለማድረጉን ያመለክታል፡፡

4. በመጨረሻም በሌላ ማጣቀሻ ማጠናከር ቢያስፈልግም፣ የተጠቀማቸው ቃላት የፀሀፊውን አፍቃሬ-ኮሙኒስትነት በመጠኑም ቢሆን ያሳያል፡፡

ፍፃሜ

——–

ማሞ እ.ኤ.አ በ1967 የሞት ፍርደኛ ሆኖ፣ ስቅላቱ ሊፈፀም ጥቂት ጊዜ ሲቀረው፣ ወደ ገመዱ በኩራት እየተራመደ በተናገረው የመጨረሻ ቃል፤

“የኔ ደም፣ ለኦሮሞ ሕዝብ መብት መከበር የሚፈስ በመሆኑ፣ በከንቱ አይቀርም፤ ባልሰራሁት ስራ፣ በሀሰት ወንጅለው የሞት ፍርድ የፈረዱብኝ ሁሉ፣ በዚህቹ ስፍራ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በቅርቡ የእጃቸውን እንደሚሰጣቸው አምናለሁ፤ በዋቃ (በእግዚአብሄር) ፍቃድ፣ በኦሮሞ ልጆች ብርታት “ጉማዬ” (የደም ካሳ) ይመለሳል፡፡ ይዋል ይደር እንጂ፣ የኦሮሞ ሕዝብ መብት፣ በልጆቹ ትግልና ጥረት መከበሩ እንደሆነ የማይቀር ነው”

(ኦላና ዞጋ፡ 428)፡፡

ቄሮ ለነፃነትህ ሰው ተከፍሎበታል!!!

***

(ከ የኦሮሞ ጉዳይ የተወሰደ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here