ይድረስ በእኔ ላይ በዘረኞቹ እና ሸፍጠኞቹ አሃዳዊያን በተከፈተው መጠነ ሰፊ ሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ግር ላላችሁ ወገኖች በሙሉ፣

0
312
Dr. Brihana Meskel Abebe Sagni

I/ የሃሰት ፕሮፖጋንዳው አላማ

1. ሰሞኑን የአሃዳዊያኖቹ ነባር እና ከለውጡ ወዲህ የተፈለፈሉ እንደ ኢትዮ 360 ያሉ ውሸታሞች እና በተለያዩ ስሞች የሚጠሩ የጩኸት ተቀባይ ጭፍሮቻቸው በአዲስ መልክ በእኔ እና በኦሮሞ ህዝብ ላይ የጀመሩት ስም የማጥፋት እና ዘረኛ ፕሮፖጋንዳቸው ተጧጥፎ ቀጥሏል።

2. የዚህ የጥላቻ እና የእኔን መልካም ስም ጭቃ የመቀባት ዘመቻው ዋና አላማ፣ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ(በተለይም ደግሞ በአማርኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን ዘንድ) የሚሰሙ እና የሚደመጡ፣ እጅግ በጣም ጥቂት የብሄር ፖለቲካ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ የኦሮሞ ሙሁራንን ስም በማጠለሸት እና ራሳቸው የተዘፈቁበትን የዘረኝነት መርዝ በመቀባት፣ የኦሮሞን ህዝብ የፍትህ ፣ የእኩልነት እና የሪዕት ጥያቄዎችን ገልብጦ “የተረኝነት” እና “የዘረኝነት” ጥያቄ በማስመሰል እና የኦሮሞ ህዝብ የእኩልነት፣ የፍትህ እና የሪዕት ጥያቄዎች “ኢትዮጵያን አፍርሶ ነፃ አገር በማቋቋም” ሳይሆን “በኢትዮጵያ ጥላ ውስጥ እንዲፈቱ” የሚጥሩ እንደ እኔ ያሉ እውነተኛ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊያንን “ዘረኛ እና ተረኛ” የሚል ቅፅል ስም በመሰጠት በአማሪኛ ተናጋሪው ዘንድ እንዳይደመጡ ፣ ጥርጣሬ መፍጠር እና ተቀባይነት እንዳያገኙ ለማድረግ የሚደረግ ከንቱ እና ባዶ ጩኸት ነው።

3. እነዚህ የአገር ነቀዞች፣ ዘረኞች እና ሸፍጠኞች ከዚህ በፊት በእኔ መሰል ቀደምት አገር ወዳዶች እና እኩልነት ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን ላይ ባካሄዱት ዘረኛ እና ስም የማጥፋት ዘመቻ ፌዴሬሽን ብቻ የጠየቁትን የኤርትራን ህዝብ ጥያቄ “መሬቱን እንጂ ህዝቡን አንፈልግም እያሉ” ገፍተው ኢትዮጵያን ባህር በር አልባ አገር አድርገዋል። የትግራይን ህዝብ ጠልተው፣ ህወሃትን ወልደዋል። ለኦሮሞ ህዝብ ትምህርት በአማርኛ(በኦሮሚኛ አይደለም) ይዳረስ ብለው የተነሱትን እነ ጄኔራል ታደሰ ብሩን እና የመጫና ቱለማ የኦሮሞ መሪዎችን ገለው፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወልደዋል። ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት እና እኩልነት ይታገሉ የነበሩትን እንደ እነ ኃይሌ ፊዳ እና ዶ/ር ሰናይ ልኬ አይነት ሰዎችን በልተው፣ ደርግን አፍርተዋል። በኦጋዴን፣ በሲዳማ፣ በጋምቤላ ወዘተ እነዚህ ጭፍን እና ዘረኛ አሃዳዊያን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በፈፀሙት ወንጀል እና ጥፋት አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት እና እኩልነት አጥቶ በህይወት እና በንዋይ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል።

4. በኦሮሞ ህዝብ ግንባር ቀደም መሪነት በመጣው የአሁኑ ለውጥ የኢትዮጵያ ህዝብ የእኩልነት፣ የፍትህ እና የርዕት ጥያቄዎች ምላሽ ካላገኙ እና አገርቷ አሁን ባለችበት ሁኔታ በሌላ አብዮት ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ከተዘፈቀች፣ የኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል አደጋ ላይ እንደሚወድቅ በቅን ልቦና ነገሮችን ለምያስተውል ኢትዮጵያዊ ሁሉ የአደባባይ ምስጥር ነው። የእኔ ይህን ለውጥ መደገፍ እና ሌሎች ለውጡን እንዲደግፉ ማበረታታትም ብቸኛው ምክንያትም፣ ይህንኑ አገራዊ አደጋ እና ስጋት ለማስቀረት እና ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን መገንባት ነው።

5. በተቃራኒው፣ በደርግ እና በህወሃት ዘመን ከአገር ፈርጥጠው አሜርካ እና አውሮፖ የከረሙት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ አሸልበው ከሞት የነቁት አሃዳዊያን ዓላማ ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን መገንባት ሳይሆን የአፄ ኃይለስላሴን ኢትዮጵያ ከመቃብር አውጥቶ፣ ሰማንያ ከመቶ የሚሆነውን አማርኛ ተናጋሪ ያልሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ጨፍልቆ ወይም አግሎ የአንድ ቋንቋ፣ የአንድ ባህል ወዘተ ኢትዮጵያን መልሶ መገንባት ነው።

6. እነኝህ ዘረኛ እና ሸፍጠኛ አሃዳዊያን፣ ቅዠታቸውን ለማሳካት የአማራ እና የኢትዮጵያን ካርዶች እየቀያየሩ ይጫወታሉ። በአንድ በኩል የአማራው ህዝብ ጠበቃ በመምሰል እና የአማራውን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ (በተለይም ከኦሮሞው ህዝብ) ለመለየት፣ አማራ ተጨቆነ የምትል ነጠላ ዜማ ያዜማሉ። በአማራ ክልል ስማቸውም፣ ስራቸውም፣ ዘፈናቸውም ይኸው ብቻ ነው።

7. በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮሚያ (አዲስ አበባን ጨምሮ) ሲደርሱ ዞር ብለው በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ ከሌላ ብሄር የመጡ አማርኛ ተናጋሪ ወገኖችን ለማጃጃል ኢትዮጵያ የምትል ካርድ ይመዙና “ኢትዮጵያ ወይም ሞት” እያሉ የዓዞ እምባ ያለቅሳሉ ። ከዚያም አልፈው ይህንኑ እስስታዊ ባህሪያቸውን ለመሸፈን፣ እነዚህ ዘረኛ እና ሸፍጠኛ አሃዳዊያ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች የኦሮሚያ ከተሞች፣ በሃረሪ፣ እና በደቡብ ኢትዮጵያ የተለያዩ የዳቦ ስሞችን ይጠቀማሉ። እንደ ጥንብ አንሳ ሰፊረውበት የሚበሉት እና አግተውት ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ልያባሉት እና ለእኩይ ዓላማቸው እንደ ዱላ ሊጠቀሙበት የሚያደራጁት ግን በነዚህ አከባቢዎች የሚኖሩትን አማርኛ ተናጋሪውን ህዝብ ብቻ ነው።

8. የእነዚህ ዘረኛ አሃዳዊያ ብቸኛ ግብ ግን፣ የአማራ ህዝብን ጥቅም ማስከበር ወይም የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ ሳይሆን፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በጋንቤላ እና በቤኒ ሻንጉል ክልሎች በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ የተፈጠሩ አማርኛ ተናጋሪ ከተሞችን ይዞ እና እንደገና አደራጅቶ፣ አማርኛ ብቻ ተናጋሪ ኢትዮጵያን እንደገና መፍጠር ነው።

9. ለዚህ ነው “ኦሮሚኛ ከአማርኛ ጋር የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ ይሁን፣ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ይከበር፣” እያልን የምንናገረውን እንደ እኔ ያሉ ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸውን የኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ሙሁራንን “ተረኛ እና ዘረኛ” ብለው፣ የራሳቸውን ትክክለኛ ስም ለእኛ ለመስጠት የሚዳዳቸው።

10. ሰሞኑንም በእኔ ላይ የተከፈተው የጥላቻ እና ስም የማጥፋት ዘመቻ ዓላማም፣ እንደ እኔ አይነት ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች መጥቃት፣ ይህንኑ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባህል፣ አንድ ሃይማኖት ያላት Assimilationist ኢትዮጵያን የመፍጠር ቅዠታቸውን ያሳካልናል የሚል ሌላ ቅዠት ነው። አለበለዚያ፣ በኢትዮጵያም ሆነ በአሜርካ በስመ ጥሩ እና ታዋቂ ዩንቨርሲቲዎች ያገኘሁት እውቀት እና በስመ ጥሩ ተቋማት(የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ) ያገኘኋቸው የስራ ልምዶች እና መልካም ስሞች፣ በእነርሱ የቁራ ጩኸት እንደማይጎድፉ፣ ወይም እነርሱ በጩኸት ብዛት ስላላባቸው የእኔ እውቀት እንደማይተን ባወቁ ነበር።

11. እኔ በኦሮሞ ህዝብም ሆነ በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ (አማርኛ ተናጋሪ ወገኖቼን ጨምሮ) ዘንድ ያለኝ መልካም ስም የተገነባው ለበርካታ አመታት የኦሮሞን ህዝብ የእኩልነት፣ የፍትህ እና የርዕትህ ጥያቄዎችን ሳልሸቃቅጥ፣ በቅድመ አያቶቼ እና ከኦሮሞ ህዝብ እንዲሁም ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች አብራክ በወጡ ጀግኖች አባቶቻችን በተገነባችው ኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት ላይ ሳላመቻምች ግልፅ እና በእውነት ላይ የተመሰረተ አቋም በጊዜውም፣ ያለጊዜው በጥናት አራምድ ስለነበረ ነው።

12. መልካም ስሜ እና በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ያለኝ መወደድ እና ተቀባይነት እንደ ወደረኞቼ ስም፣ በህዝብ ገንዘብ ስርቆት የተገዛ፣ ወይም የኢትዮጵያን ህዝብ ደም በማፋሰስ እና በማባላት በደም በተጨማለቀ እጆች የተገነባ ስም ሳይሆን፣ የእግዚኣብሄር ፀጋ በዝቶልኝ ከልብ በእውነት እና በእውቀት ለህዝብ እና ለአገር ከመስራት የመጣ ነው። ባለፉት በርካታ ዓመታት፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ባበረከትኩት አስተዋፆ የጎዳሁት ራሴን እና ቤተሰቤን ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ የአንድም ሰው ሆነ የማንም ቡድን ዕዳ የለብኝም። የእኔ እና የቤተሰቤ ጉዳት እንዳለ ሆኖ፣ በእኔ አስተዋፆ የኢትዮጵያ ህዝብ ከተጠቀመ፣ እኔም ሆንኩኝ ቤተሰቤ እንደ ትርፍ እንቆጥረዋለን።

II /የአሃዳዊያን የጦርነቱ ሞዴል እና የተራማጅ ኃይሎች ማሸነፊያ መንገድ፣

13. ሶስት ነገር ብዬ ፁሁፎን አጠቃልላለሁ። እነዚህ ዘረኛ እና ሸፍጠኛ አሃዳዊያን፣ በኢትዮጵያ እኩልነት፣ ፍትህ እና ርዕትህ አንዳይሰፍን እና ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የእኩል አገር እንዳትሆን ሶስት ጣምራ ጦርነቶችን እያካሄዱ መሆኑን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተገንዝቦ ከነዚህ ዘረኞች እና ሸፍጠኞች እራሱን መከላከል አለበት።

14. በተለይም ደግሞ፣ የነዚህ ጦርነቶች ጦር ሜዳ እንዲሆን የዘረኞቹ ግንባር ቀደም ጠላት ተደርጎ የተፈረጀው የኦሮሞ ህዝብ ቀጥዬ በማስቀምጣቸው በሶስቱም የጦርነት ዘርፎች አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት፣ ራሱንም ሆነ በኢትዮጵያ እኩልነት እና ፍትህ እንዲሰፍን የሚታገሉ ኢትዮጵያዊያንን አደራጅቶ፣ በተቀናጀ እና በተማከለ መልኩ ጦርነቱን አሸንፎ፣ አዲስቷን ኢትዮጵያን ለመገንባት መነሳት አለበት።

15. እነዚህ ዘረኛ እና ሸፍጠኛ አሃዳዊያን የአንድ ቋንቋ፣ የአንድ ባህል እና የአንድ ሃይማኖት የበላይነት የተረጋገጠበት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ባላቸው ከንቱ ቅዠቶች የተለሟቸው እና በግልፅ እያካሄዱ ያሉት ሶስት ጣምራ ጦርነቶች የሚከተሉት ናቸው።

15. 1/ አንደኛው የኣሃዳዊያኑ የጦርነት ስልት በኢትዮጵያ እኩልነት፣ ፍትህ እና ርዕትህ እንዲሰፍን የሚታገሉ የለውጥ መሪዎችን፣ ሙሁራንን፣ አክቲቭስቶችን፣ ባለሃብቶችን፣ እና እንደ ኦሮሞ፣ ሲዳማ ወዘተ ያሉ ህዝቦችን በቀጥታ ማጥቃት(Direct Violence) አንዱና ዋነኛው የትግል ስልት ነው። እነዚህ ዘረኛ እና ሸፍጠኛ አሃዳዊያን በቀጥታ በሚያካሄዲት ጦርነት(Direct war) ለእኩልነት፣ ለፍትህ እና ለርዕትህ የሚታገሉ በለውጥ አመራሩ ውስጥ ባሉ ሰዎች፣ ተራማጅ ቡድኖችን እና ህዝቦችን 1ኛ) ዘረኛ፣ 2ኛ) ተረኛ፣ 3ኛ) ጠባብ፣ ጎጠኛ፣ ጎሰኛ፣ 4ኛ) ፀረ ኢትዮጵያ እያሉ ስም ማጥፋት እና በአካል ማጥቃትን ይጨምራል። በእኔም ላይ የተከፈተው ዘመቻ የዚሁ ቀጥተኛ ጦርነት አካል ነው። ለዚሁ አላማም ወደ መቶ የሚሆኑ ስም ማጥፊያ፣ ውሸት እና ጥላቻ ማምረቻ የፕሮፖጋንዳ ሚዲያዎችን አቋቁመዋል። በኦሮሚያ ያሉ አማርኛ ተናጋሪዎችን እያደራጁ እና ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ማጋጨት እና ማባላት ላለፉት ሁለት ዓመታት በግልፅም፣ በስውርም ሲሰሩት የነበሩ የዚህ ቀጥተኛ ጦርነት(direct violence) አካል ናቸው። በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሲዳማ የተከሰቱት ግድያዎች የነዚህ ዘረኞች እና ሴረኞች የቀጥታ ጥቃት(direct violence) ውጤት ነው።ለውጡ ሙሉ በሙሉ ተቀልብሶ የፖለቲካ እና የፀጥታ መዋቅሩ በነዚህ አሃዳዊያን እጅ ከወደቀ፣ በኢትዮጵያ ከ1966ቱ አብዮት ማግስት ከነበረው የነጭ ሽብር እና የቀይ ሽብር እልቂት የከፋ ዕልቂት በኢትዮጵያ እንደሚፈጠር፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ማወቅ አለበት። በኢትዮጵያ እኩልነት፣ ፍትህ እና ርዕትህ እንዲሰፍን የሚታገሉ የለውጥ ኃይሎችን አሰባስቦ ማደራጀት እና ኢትዮጵያን ወደ ፊት ማራመድ እና ከነዚህ ሴረኞች የእልቂት ድግስ ማዳን፣ የሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ቅዳሚ ተግባር መሆን አለበት።

15. 2/ ሁለተኛው የሴረኞቹ አሃዳዊያን ጦርነት፣ በኢትዮጵያ እኩልነት፣ ፍትህ እና ርዕትህ እንዲሰፍን በሚታገሉ እንደ ኦሮሞ፣ ሶማሌ፣ ሲዳማ እና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ላይ መዋቅራዊ የሆነ ጦርነት (structural war) ማካሄድ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በተለይም አሁን የመጣውን ለውጥ በግንባር ቀደምትነት የመራው የኦሮሞ ህዝብ ማወቅ ያለበት፣ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ፣ የደርግ እና የህወሃት መንግስታት መጥተው ይሂዱ እንጂ፣ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን በተገነባው ቢሮክራሲ፣ የከተማ መዋቅር፣ የሃይማኖት ተቋማት መዋቅር፣ የኢኮኖሚ መዋቅር፣ የባህል መዋቅሮች፣ የሚዲያ መዋቅሮች እና የመንግስት መዋቅሮች ላይ የቆመች ነች።

እነዚህ ሁሉ መዋቅሮች(structures and institutions) ደግሞ የተሞሉት እና ተጠፍንገው የተያዙት በኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች እና ታርኮች እኩልነት በማያምኑ፣ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ፍትህ እና ርዕትህ እነዲሰፍን በማይፈልጉ፣ ፀረ ኢትዮጵያ እና ፀረ እኩልነት፣ ዘረኛ እና ሸፍጠኛ አሃዳዊያን ነው።

አሁን ከለውጡ ማግስት፣ እነዚህ አሃዳዊያን እና ተከታዮቻቸው፣ በደርግ እና በህወሃት ዘመን ካደቡበት ቦታዎች ሁሉ ለውጡ ባመጣው ቀዳዳ እና ዕድል ከተሰባሰቡ በኋላ፣ ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገር፣ ያለ ያሌለ ኃይላቸውን አስተባብረው የአፄ ኃለስላሴውን ዘመን መዋቅሮች activate በማድረግ ፣ በኢትዮጵያ እኩልነት፣ ፍትህ እና ርዕትህ እንዲመጣ በታገለው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መጠነ ሰፊ መዋቅራዊ ጦርነት(structural war) ከፍተዋል።

አሁን ከለውጡ በኋላ ያሉትን የኢትዮጵያ መዋቅሮች ስነልቦና አስተውሎ ላየ፣ ከአፄ ኃይለስለሴ ጊዜ በባሰ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት ቢሮክራሲ፣ የከተሞች መዋቅር፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የባህል ተቋማት፣ የኢኮኖሚ ተቋማት፣ እና የፖላቲካ ተቋማት ከአንድ ቋንቋ እና ባህል ውጭ ያሉት ወደ ሰማንያ ከመቶ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚገለሉበት (discriminate የሚሆኑበት) እና የሚገፉበት (unwelcome) የሚደረጉበት አዝማሚያ በከፍተኛ ደረጃ እየተቀናጀ እና የተደራጀ መዋቅራዊ ዘመቻ (structured compaign) ፣ ትልቅ ገንዘብ እና የሰው ኃይል ተመድቦላቸው እየተካሄደ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው።

ለምሳሌ፣ በነዚህ ፀረ -እኩልነት እና ፀረ-ኢትዮጵያ አሃዳዊያን በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚደረጉትን ” የኦሮሞ ዘረኞች እና ተረኞች ላይ የተከፈተ መዋቅራዊ ጦርነት” ብለው በሰየሙት መዋቅራዊ ጦርነት (structural war) ባህሪ እንመልከት። የጦርነቱ ትርክት የተቃኘው፣ “ኢትዮጵያ በወሮሞዎች ተወራለች” በማለት ነው። የወረራ ትርክቱ የተቀዳው አባ ባህሬ የሚባል መነኩሴ በ16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ኦሮሞ፣ መዳ ወላቡ ከሚባል ውሃ ውስጥ ወቶ ኢትዮጵያን ወረራት ከሚል ሃሰተኛ ተረት ነው። አሃዳዊያኑ አሁን “ዘረኞች እና ተረኞች” ኢትዮጵያን ወረሩ ሲሉ ከአራት መቶ አመት በላይ የቆየውን የኦሮሞ ጥላቻ ለመቀስቀስ እና ኦሮሞ በኢትዮጵያ መጤና ባለአገር አይደለም ለማለት እንጂ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ጎንደር እና ጎጃም የሾመው አንድም ኦሮሞ ያሌለ መሆኑን ሁሉም አሳምረው ያውቃል። ቢኖርም እንኳ፣ ደጉ እና ጨዋው የጎንደር እና የጎጃም ህዝብ ግድ የለውም።

የአሃዳዊያኑ “የዘረኞች እና የተረኞች ጦርነት” የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ የመንግስት ቢሮክራሲ፣ የፖላቲካ መዋቅር ፣ የኢኮኖሚ መዋቅር፣ የኃይማኖት መዋቅር፣ የባህል መዋቅር እና የሚዲያ መዋቅር ውስጥ ምንም አይነት ውክልና እንዳይኖረው ማድረግ ነው። አሃዳዊያኑ በዚህም ሂደት በሚያደርጉት systemic ጦርነት የመጀመሪያው ግብ፣ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ ከኢትዮጵያ መዋቅሮች ተገሎ የቆየው ሰማንያ ከመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ ከስረዓቱ አግሎ ማቆየት ሲሆን፣ ሁለተኛው ግብ ይህ ህዝብ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት የእኩልነት፣ የፍትህ እና የርዕትህ ጥያቄዎችን አልመለሰም ብሎ ጠቅላይ ሚንስትሩ የህዝብ ድጋፍ እንዲያጡ፣ እና መንግስታቸው ተዳክሞ እንዲወድቅ፣ ይጥራሉ። አንዳንዶች ይህን የአሃዳዊያን መዋቅራዊ ጦርነት( structural war) የአፄ ምንልክን ፖሮጀክት መጨረስ ይሉታል።

በኢትዮጵያ እኩልነት፣ ፍትህ እና ርዕትህ እንዲሰፍን የሚታገሉ ኢትዮጵያዊያን ይህን መዋቅራዊ ጦርነት ለማሸነፍ አሃዳዊያን የሞሉበትን እና ያበሰበሱትን ያረጀ አግላይ መዋቅር(old and discriminatory governance software) ለማስተካከል ከመጣር፣ አሮጌውን መዋቅር ከነትብታቡ ቆሻሻ መጣያ ውሥጥ ጥሎ፣ አዲስ እና ሁሉን አቀፍ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን መዋቅር (new and all inclusive governance software) በአገርቷ ላይ እንደ አዲስ መጫን ነው። በ1966ቱ እና በ1983ቱ ለውጦች አሮጌውን የአፄ ኃይለስላሴ Imperial Ethiopianን መዋቅሮች ጠጋግኖ እና ጉልቻ(ሰው) ቀያይሮ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር መጣር፣ ኢትዮጵያን የበለጠ አዳከማት፣ አፈራረሳት እንጂ አላሳደጋትም። የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ የለውጥ ኃይሎች ቀጣይ ዓላማ ይህንኑ የአስተዳደር software መቀየር መሆን አለበት።

15. 3/ ሶስተኛው የዘረኛና የሸፍጠኛው የአሃዳዊያን ጣምራ ጦርነት በኢትዮጵያ እኩልነት፣ ፍትህ እና ርዕትህ በሚፈልጉ ተራማጅ (progressive) ኢትዮጵያዊያን ላይ የስነ ልቦና እና የባህል ጦርነት (cultural war) ማካሄድ ነው። ይህ ባህላዊ ጦርነት የሚካሄደው በተራ ተከታዮቻቸው ውስጥ አሃዳዊያኑ የሚያካሄዱት ዘረኝነት እና አግላይነትን ባህላዊ እንዲሆን እና ቅቡልነት እንዲኖረው በማድረግ ነው። ለምሳሌ፣ በተራው ተከታዮቻቸው ዘንድ የአሃዳዊያኑን ቋንቋ መናገር ኢትዮጵያዊ የሚያስብል እና ተናጋሪው የሚኮራበት ሲሆን፣ ሌሎች እንደ ኦሮሚኛ፣ ሲዳሚኛ እና ሶማልኛ የመሳሰሉትን ቋንቋዎች መናገር ደግሞ ዘረኝነት እና ተናጋሪውን የሚያሸማቅቁ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

በሌላ በኩል ለምሳሌ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችን እኩልነት የሚናገሩ ከሉ ” እባክህ ሰው ሁን” ይላሉ። ይህ ማለት ከእነርሱ ብሄር ውጭ ያለው ሌላው ብሄር ሰው አይደለም ማለት ነው። ዘረኞቹ አሃዳዊያን ይቺን “እባክህ ሰው ሁን” የምትለውን ትርክት የቀዱት ከነጭ ዘረኞች መፅሃፍ ነው። ነጮች ጥቁሮችን በባርነት ሲሸጡ፣ የዋሁ ተራ ነጭ ህዝብ የጥቁሮችን ባርነት እንዲቀበል እና የባርያው ስረዓት እንዲቀጥል፣ ጥቁሮች ሰው አይደሉም ወይም ሙሉ ሰው አይደሉምሉ የሚለው አመለካከት ባህል እንዲሆን አድርገው ነበር። በነጩ ብቻ ሳይሆን በመላው አለም ጥቁሮችን የመናቁ እና የመጥላቱ አመለካከት አለም አቀፋዊ የሆነው ከዚሁ ነጮች ከፈጠሩት በጥቁር ህዝብ ላይ ከተፈጠረ ባህላዊ ጦርነት(cultural war) ነው። የእኛዎቹ እንጭጭ አሃዳዊ ዘረኞችም ይህን ነጮቹ ዘርተው መንቀል ያቃታቸውን የባህል ጦርነት (cultural violence) ኢትዮጵያ ውስጥ በመዝራት የዋሁን የኢትዮጵያን ህዝብ እርስ በርሱ ልያባሉት ሌት ተቀን ይጥራሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ እኩልነት፣ ፍትህ እና ርዕትህ እንዲሰፍን የሚታገሉ ተራማጅ እና የለውጥ ኃይሎች የነዚህን ዘረኛ እና ሸፍጠኛ አሃዳዊያን ግልፅ እና ስውር ጦርነቶች በየደረጃው በመለየት እና ስር ሳይሰዱ ማፍረስ አለባቸው። ከላይ ካስቀመጥኩት አሃዳዎያኑ ከከፈቱብን ጦርነቶች ከመጀመርያው ቀጥተኛ ጦርነት(direct war) ውጭ ያሉት መዋቅራዊ(structural) እና ባህላዊ (cultural) ጦርነቶች በአብዛኛው ህዝባችን ዘንድ በደንብ የማይስተዋሉ፣ በግልፅ ቶሎ የማይታዩ፣ ነገር ግን ህዝባችንን ከስሩ ነቅለው ያጠፉ እና እያጠፉ ያሉ የኣሃዳዊያኑ ዘረኛ መዋቅሮች ናቸው። እነዚህን አግላይ እና ዘረኛ መዋቅሮች አፍርሶ፣ በሌላ ለሁሉም የእኩል በሆነ እና ሁሉን አቃፊ መዋቅር የመተካት ድርሻ የዘረኛ አሃዳዊያኑ ሳይሆን ለእኩልነት፣ ለፍትህ፣ እና ለርዕትህ የሚታገሉት ተራማጅ ኢትዮጵያዊያ እና የለውጥ ኃይሎች ግንባር ቀደም ስራ እና ኃላፊነት ነው። ሃላፍነታቸውንም መወጣት አለባቸው። የመኖር እና ያለመኖር ግዴታቸውም ነው።

በሌላ በኩል፣ እነዚህ ዘረኛ ኣሃዳዊያን ፀረ እኩልነት ብቻ ሳይሆኑ ፀረ ኢትዮጵያ አንድነት ስለሆኑ፣ ተራማጅ እና ለእኩልነት የቆሙ የለውጥ ኃይሎች ለረጅም ጊዜ የነዚህ ኃይሎች መቀለጃ የሆነውን የኢትዮጵያን ካርድ እና የኢትዮጵያን ስም ከእነኚህ ዘረኛ እና ሸፍጠኛ አሃዳዊያን እጅ መቀማት አለበት። የኢትዮጵያ ስም በማይገባቸው እና በማይገባቸው እጅ መቀለጃ መሆን የለበትም። የኢትዮጵያን ስም በሚገባቸው እና በሚገባቸው እጅ የማኖሪያው እና ሱሙን እንደገና ማደሻው ጊዜው አሁን ነው።

III/ ማጠቃለያ፣

16. ለማጠቃለል ያህል፣ ሰሞኑን ለአንድ ሳምንት፣ ሌሎቹም ባለፉት ሁለት አመታት የዘረኝነታቸው እና የስም ማጥፋት ዘመቻ ዒላማቸው ያደረጉኝ በግል ስለሚያውቁኝ አይደለም። አንዳቸውንም በአካል አላውቅም። አያውቁኝም። ነገር ግን እነዚህ ቡድኖች፣ የዘረኛው እና ሸፍጠኛው አሃዳዊያኑ ወታደሮች እና ወሮ በሎች ናቸው። ስንቅ እና ትጥቅ የሚሰፉሩላቸው እነዚሁ ይህ ለውጥ እንዲደናቀፍ፣ ወይም እንዲጠለፍ የሚሹ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ እኩልነት፣ ፍትህ እና ርዕትህ ላይ የተመሰረተ ስረዓት እንዲፈጠር ፈፅሞ የማይሹ አሃዳዊያን ናቸው። ጦርነቱም፣ በእኔ በግሌ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ እኩልነት፣ ፍትህ እና ርዕትህ እንዲሰፊን በሚታገሉ ተራማጅ እና የለውጥ ኃይሎች ሁሉ ላይ ነው። ትግሉ ይቀጥላል። ለውጡም አይቀለበስም። እንደምናሸንፍም ጥርጥር የለውም። በሰላም ቆዩኝ። መልካም የትንሳኤ በዓል!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here